ቀጥታ፡

የቻይና ሻንዚ ግዛት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውን የማጠናከር ፍላጎት አላቸው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦የቻይና ሻንዚ ግዛት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እንደሚፈልጉ የግዛቷ ምክትል ገዥ ዋንግ ዢኦ ገለጹ።

የኢትዮጵያና ቻይና የኢኮኖሚና ንግድ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረ ሲሆን በፎረሙ በርካታ የቻይናና የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ተገኝተዋል።


 

በቻይና ሻንዚ ግዛት ምክትል ገዥ ዋንግ ዚኦ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያና ቻይና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ አጋርነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

ሻንዚ ግዛት የጥንታዊ ቻይና ስልጣኔ መነሻ፣ የኢኖቬሽንና ፈጠራ ማዕከል እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ የቻይና ሻንዚ ግዛት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ይፈልጋሉ ብለዋል።

ግዛቷ ተፈጥሮ ጋዝን ጨምሮ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት እንዳላት ጠቅሰው፤ ለጋራ ተጠቃሚነታችን በጋራ እንሰራለን ብለዋል።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የግብርና የኢንዱስትሪና የማዕድን ምርቶችን በስፋት ወደ ቻይና እንደምትልክም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓን ተከትሎ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለግል ባለሃብቱ ክፍት ማድረጓን ተናግረዋል።

የቢዝነስ አማራጮችን በማስፋት ከስትራቴጂክ አጋር ሀገራት ጋር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በርካታ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አንስተዋል።


 

ኢትዮጵያ በርካታ የህዝብ ቁጥር ያላት ከመሆኑም በላይ ለገበያ ምቹ የሆነ ስትራቴጂክ ቦታ ላይ መቀመጧንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በጋራ የመልማት ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል።

የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ ኤዥያና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር  ሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ያልተቋረጠ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በተለይም ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ወዳጅነታቸውን የበለጠ አጠናክሮታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም