በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጤና ጣቢያዎች የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጤና ጣቢያዎች የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው
ጂንካ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና ጣቢያዎችን የሕክምና አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ ለግብአትና ለሰው ሃይል ማሟላት ሥራ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በ13 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የኦሞራቴ ጤና ጣቢያ መለስተኛ ቀዶ ሕክምና መስጫ ማዕከል እና ሞዴል የማህበረሰብ ፋርማሲ ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ጋርሾ በወቅቱ እንደገለፁት መንግስት ለህብረተሰቡ ፍትሀዊ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።
ለዚህም መንግስት በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማትን በግብአትና በሰው ሀይል ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትና የማህበረሰብ ፋርማሲን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የጤና ጣቢያዎችን ተደራሽነት በማሳደግ ለተሻለ ህክምና ወደ ሆስፒታሎች በሚደረግ ጉዞ በታካሚዎች ላይ የሚደርስን እንግልትና ተጨማሪ ወጪ ለማስቀረት አሰራር መዘርጋቱንም አቶ ማቲዎስ ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በ13 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት የኦሞራቴ ጤና ጣቢያ የመለስተኛ ቀዶ ህክምና መስጫ ማዕከል እና ሞዴል የማህበረሰብ ፋርማሲ የዚሁ አካል መሆናቸውን አንስተዋል።
የዳሰነች ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ግርማ፣ በወረዳው የተገነባው የቀዶ ሕክምና መስጫ ማዕከል ቀደም ሲል ለተሻለ የሕክምና አገልግሎት ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚደረገውን ጉዙ ማስቀረቱን ተናግረዋል።
ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት በቅርበት በመስጠት የእናቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኡሪ በለከች የማዕከሉ ወደሥራ መግባት የተሻለ ሕክምና ለማግኘት ወደሌላ አካባቢ ሲሄዱ ይደርስባቸው የነበረን እንግልት እንደሚያስቀር ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ባለመኖሩ ለወጪ ሲዳረጉ እንደነበረና ማዕከሉ ይህንንም ችግር እንደሚፈታላቸው ገልጸዋል።
በዳሰነች ወረዳ ሞዴል የማህበረሰብ ፋርማሲ ምረቃ ላይ የተገኙት የወረዳው ነዋሪ አቶ በትግሉ ጌታሁን በበኩላቸው በጤና ተቋማት በሚያጋጥም የመድኃኒት እጥረት ምከንያት ለተጨማሪ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
አንዳንድ መድሀኒቶች በቅርበት እንደማይገኙ ጠቁመው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት መንግስት የማህበረሰብ ፋርማሲ ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱ የመድኃኒት እጥረቱን በእጅጉ ያቃልለዋል ብለዋል።
በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞኑ አመራር አባላት፣ አጋር ድርጅቶች እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።