ሮማኒያ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት - አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ - ኢዜአ አማርኛ
ሮማኒያ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት - አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2018(ኢዜአ)፦ሮማኒያ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ ኢትዮጵያ እና ሮማኒያ በጋራ የሚሰሩባቸው ዘርፈ ብዙ አቅሞች መኖራቸውን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መሆኑን ገልጸው፤ በፈጣን የልማት ጎዳና ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በርካታ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለውጭ ኢንቨስትመንት እየከፈተች መሆኗ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ይህም ሮማኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ ትብብር አብራ እንድትሰራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ሀገራቸው የተፈጠረውን ዕድል ለመጠቀምና በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ሮሚኒያ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ በአውሮፓ ተጠቃሽ ሀገር መሆኗን ያነሱት አምባሳደሯ፥ ኢትዮጵያም ዲጂታላይዜሽንን እያስፋፋች መሆኗ በዲጂታል ዲፕሎማሲ አብሮ የመስራት ዕድል መኖሩን ጠቅሰዋል።
በትምህርት ረገድ ኢትዮጵያና ሮማንያ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው በማንሳት፥ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሮማኒያ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው ሲማሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በትምህርት ልማት ሁለቱ ሀገራት ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ሮማኒያና ኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነት እንዳላቸው በመግለፅ፥ የተፈረሙ ፕሮቶኮሎችን በመጠቀም የንግድና የዘርፍ ማህበራት የትብብር ማዕቀፍ ለማዘጋጀትና መድረኮችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንትና የአጠቃላይ የኢኮኖሚ ምህዳር ለውጥ መኖሩን ገልጸው፥ ሮማኒያም የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሯን ለማጠናከር ጊዜው አሁን ነው በሚል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።