ቀጥታ፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ እንደሚደግፉ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ):-የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሆኑት ሲቲ እና ጄፒ ሞርጋን የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ልማት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን የአሜሪካ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሆኑት ጄፒ ሞርጋን እና ሲቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

የሲቲ የመንግስት የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄይ ቫርኪይ እና የጄፒ ሞርጋን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኦሊቨር ኢዌክ በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።


 

ውይይቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ፣የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና ዘላቂ የኢንቨስትመንት ኢኒሼቲቮች መደገፍ የሚቻልባቸው የፋይናንስ አማራጮች ላይ ያተኮረ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፥ እየተደረጉ ስላሉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ገለጻ አድርገዋል።

መንግስት የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና በዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያዎች ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት ጥረቶች እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አቶ አሕመድ ለሁለቱ ተቋማት አመራሮች የኢትዮጵያን ዘላቂ እዳ አስተዳደር የመፍጠር ጥረቶች፣የውጭ ምንዛሬ ገበያ ሪፎርሞች እና የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ትግበራ አስመልክቶም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የመሪ ልማት እቅዱ በግሉ ዘርፍ የሚመራ እድገት እና አረንጓዴና ሁሉን አቀፍ ልማት እውን ማድረግን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ አጋሮች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና የማይበገር አቅም የመገንባት ስራ በመደገፍ ረገድ ያላቸውን ቁልፍ ሚና አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የሲቲ እና የጄፒ ሞርጋን ከፍተኛ አመራሮች የፋይናንስ ተቋማቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የመንግስት፣የግሉ ዘርፍ እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ካፒታል በማጣመር የኢትዮጵያን የልማት ትኩረቶች መደገፍ የሚቻልባቸውን እድሎች እንደሚመለከቱም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ፣ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ታዳሽ ኃይል፣ የካፒታል ገበያ ልማት እና ተመጣጣኝና የረጅም ጊዜ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል የሚያስችሉ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት ሌሎች ውይይት የተደረገባቸው አጀንዳዎች።

ሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ልማት እና የፋይናንስ መዋቅሮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ደረጃና የቴክኒክ ውይይቶችን ለማድረግና ትብብራቸውን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም የፋይናንስ ገበያ ጋር የበለጠ እንድትተሳሰር በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውንም የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም