በባሕርዳር ከተማ ከሕብረተሰቡ ጋር የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በባሕርዳር ከተማ ከሕብረተሰቡ ጋር የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን አስችሏል

ባሕርዳር፤ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ) ፡-በባሕርዳር ሕብረተሰቡን በማስተባበር የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ማስቻሉን የከተማው አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ።
በአማራ ክልል በየደረጃው ሲካሄዱ በቆዩ ሕዝባዊ ውይይቶች ሕብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ሰላምን ለማጽናት ያለውን የፀና አቋም በተግባር እያሳየ ነው።
ይህንን በቁርጠኝነት በተግባር እያሳዩ ካሉት የክልሉ አካባቢዎች መካከል ባሕርዳር ከተማ ይጠቀሳል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ ከባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ጌትነት አናጋው ጋር ቆይታ አድርጓል።
ኃላፊ እንደገለጹት፥ ሕብረተሰቡ ከፀጥታ አካሉና ከአመራሩ ጋር ተቀራርቦ፣ ተናቦና ተቀናጅቶ በመስራቱ ከተማዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ አስችሏል።
ቀደም ሲል የፅንፈኛው ተላላኪዎች ዘረፋ፣ ስርቆትና እገታ በመፈፀም ሕዝቡን ለችግር ሲያጋልጡ እንደቆዩ አውስተዋል።
ከከተማው ማሕበረሰብ ጋር በመተባበር በተከናወነው ቅንጅታዊ ስራ አጥፊዎችን በመለየት የሕግ የበላይነት ተከብሮ በከተማው ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸዋል።
አመራሩና የፀጥታ መዋቅሩ ከወጣቶች፣ሴቶች፣ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀትና በማወያየት ሰላም የፀና እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተን በመስራታችን በከተማዋ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት፣የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታና ሌሎች የልማት ተግባራትን በማከናወን ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉም ተናግረዋል።
በቀጣይም በከተማዋ የሰፈነውን አስተማማኝ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል ከማሕብረተሰቡ ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ጎልብቶ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በየአካባቢው የተቋቋሙ የማሕበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ማዕከላትን በማጠናከር፣ የሰላም አስከባሪና የሚሊሻ ኃይሉን አቅም በመገንባትና በሎጂስቲክስ በመደገፍ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ አብራርተዋል።