የጀርመኑ ግዙፍ ኩባንያ ባየር በኢትዮጵያ በመድኃኒት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የጀርመኑ ግዙፍ ኩባንያ ባየር በኢትዮጵያ በመድኃኒት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ)፦ የጀርመኑ ግዙፍ የፋርሚሲዩቲካል እና ባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባየር በኢትዮጵያ በመድኃኒት ማምረት ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከጀርመኑ የፋርሚሲዩቲካል እና ባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባየር ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢል አንደርሰን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የመድኃኒት ዘርፍ(ፋርማሲዩቲካል) ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችና አጋርነት መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ያላትን ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረቶችና ተነጻጻሪ ጥቅሞች ያነሱ ሲሆን በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እና ህዝብ እድገት እያስመዘገበች ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።
መንግስት የመድኃኒት ምርትና ማከፋፈልን ጨምሮ በተለያዩ ግዙፍ መስኮች ለሚሰመሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
ውይይቱ ሌላኛው ያተኮረበት ጉዳይ በኢትዮጵያ ያለውን የመድኃኒት ግብዓቶች የማምረት አቅም ማጠናከር ላይ ትብብር መፍጠር የሚቻልባቸውን መስኮች ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በመድኃኒት ዘርፍ ያላትን ስትራቴጂካዊ ስፍራና የሎጂስቲክስ አቅሞች አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ የካርጎ ኔትወርክ እና ኢትዮጵያ የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል(አፍሪካ ሲዲሲ) ዋና መቀመጫ መሆኗን በማሳያነት የጠቀሱ ሲሆን ይህም ሀገሪቱን በቀጣናው የመድኃኒት ማምረትና ስርጭት ማዕከል እንደሚያደርጋት አመልክተዋል።
አቶ አሕመድ የመንግስት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የመድኃኒት ማኑፋክቸሪንግ ላይ በሚሰራው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከታክስ ነጻ ማበረታቻ እንዲሁም የባለሀብቶችን መተማመን የሚገነባና ጥራትን የሚያረጋግጥ የሕግ ማዕቀፍ እየተገበረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የባየር ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢል አንደርሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያን መንግስት ራዕይ ያደነቁ ሲሆን ኩባንያው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ኩባንያው ኢትዮጵያ መሰረታዊ የመድኃኒት ምርቶችን ለማስፋት እያደረገች ያለውን ጥረት ለመደገፍና የፋርማሲዩቲካል ዘርፉን አቅም ለማጠናከር ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎች የመመልከት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።