ቀጥታ፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ የአርሰናል እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጨዋታ ይጠበቃል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2018 (ኢዜአ):- በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሶስተኛ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።

አርሰናል እና አትሌቲኮ ማድሪድ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾች ትኩረት አርፎበታል።  

ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በአውሮፓ መድረክ የተገናኙት እ.አ.አ በ2017/18 በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ነበር።

በወቅቱ በኤምሬትስ በተካሄደው ጨዋታ አንድ አንድ አቻ ተለያይተው በመልሱ ጨዋታ አትሌቲኮ በሜዳው 1 ለ 0 በማሸነፍ በድምር ውጤት ለፍጻሜ አልፏል። 

የማድሪዱ ክለብ በፍጻሜው ማርሴይን በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳቱ አይዘነጋም። 

በሊግ ምዕራፍ የደረጃ ሰንጠረዥ አርሰናል በስድስት ነጥብ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ በሶስት ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

አርሰናል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ19 ነጥብ  እየመራ ሲሆን አትሌቲኮ ማድሪድ አትሌቲኮ ማድሪድ በ16 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። 

የ44 ዓመቱ ጣልያናዊ ዳቪዴ ማሳ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል። 

በሌሎች መርሃ ግብሮች በቤይ አሬና ባየር ሌቨርኩሰን የወቅቱን የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂን ምሽት 4 ሰዓት ላይ ያስተናግዳል።

ቪያሪያል ከማንችስተር ሲቲ፣ ኮፐንሃገን ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከቤኔፊካ፣ ፒኤስቪ አይንድሆቨን ከናፖሊ እና ዩኒየን ሴይንት ጊሎይስ ከኢንተር ሚላን በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባርሴሎና ከኦሎምፒያኮስ እና ካይራት አልማቲ ከፓፎስ በተመሳሳይ ምሽት 1 ሰዓት ከ45 ላይ የሚካሄዱ ጨዋታዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም