መንግስት ሰላም የማስፈን ተግባርን ከልማት ስራዎች ጋር አስተሳስሮ በማስኬድ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መስራቱን ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ሰላም የማስፈን ተግባርን ከልማት ስራዎች ጋር አስተሳስሮ በማስኬድ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መስራቱን ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018 (ኢዜአ):- መንግስት ሰላም የማስፈን ተግባርን ከልማት ስራዎች ጋር ጎን ለጎን በማስኬድ የኢትዮጵያን ብልጽግና የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀድሞ እና በሥራ ላይ ካሉ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም ለልማት መሰረት መሆኑን በማመን ሰላም እንዲሰፍን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሰላም እስኪመጣ ዝም ብለን አንቀመጥም ሰላም እስኪመጣ እናለማለን፣ ምርጫችን ሰላም እያጸኑ እያለሙ መቀጠል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአንድ እጃችን ሰላምን እያስጠበቅን በሌላኛው ማልማት ካልቻልን የምንመኘውን ሰላም ማምጣት እና ማጽናት አንችልም ብለዋል።
ሰላም ከልማት ውጪ አይጸናም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ልማት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ረገድም የየአካባቢውን ጸጋ አውጥተን ስንጠቀም እና የስራችን ውጤት ሲደመር እጅግ ያማረች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንችላለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።