ቀጥታ፡

የባሌ ዞን በርካታ መስህቦችን በአንድ ቦታ የያዘ የተፈጥሮ ኃብት ነው - አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ):- የባሌ ዞን በርካታ መስህቦችን በአንድ ቦታ የያዘ የተፈጥሮ ኃብት ነው ሲሉ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከቀድሞ እና በሥራ ላይ ካሉ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱሪዝም ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ኢትዮጵያ ለማደግና ለመበልጸግ የሚያስችል ሁሉም የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

ባለን የተፈጥሮ ኃብት መለወጥና ማደግ የነበረብን ትናንት ነበር ነገር ግን የአመራር ቁርጠኝነት አልነበረም ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ለልጆቹ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ የሚጥር ትውልድ መፈጠሩንና ለዚህም የባሌ ዞን ልማት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ባሌ ውስጥ የመልማት አቅም እንዳለ በማንሳት ለግብርና የሚመች መልክዓ ምድር መኖሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን የተፈጥሮ ሃብትና የመልማት አቅም ከዞኑ ባለፈ ከድህነት ለመውጣት መጠቀም እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡

አካባቢው ለቱሪዝም ምንጭነት የሚውል ውብ መልክዓ ምድር ያለው እና በርካታ መስህቦችን በአንድ ቦታ የያዘ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሀገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሰሩ ትልልቅ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋ የሰጡና የአመራር ቁርጠኝነት የታየባቸው እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ሀገሪቱ ያላትን ሃብት በሁሉም ዘርፍ በመጠቀም ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ ሀገር የማውረስ ኃላፊነት አለበት ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም