ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ እየጸናች ትቀጥላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ እየጸናች ትቀጥላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ያለ ጥርጥር በትውልድ ቅብብሎሽ ፀንታ ትቀጥላለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ‘የሶፍ ኡመር ወግ’ ከቀድሞ እና በሥራ ላይ ካሉ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ይሄን ሁሉ ጸጋ እና ሀብት ይዘን መለመናችን እጅጉን የሚያስቆጭ እና ልንቀይረው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ታሪክ ቀይራ እንድትበለጽግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ያለ ጥርጥር ትውልድ ተቀባብሎ የሚያጸናት ሀገር ትሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ጉዳዮች መልክ እየያዙ ይመጣሉ ሲሉም ገልጸዋል።
ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሁሉም በየአካባቢው ያለውን ሀብት እያወጣ ማልማት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የሚበጀን በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በመተጋገዝ እና ተካፍሎ በጋራ መኖር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትብብር መንፈስ ከሰራን የምንመኘውን ሰላምና ብልጽግና ማምጣት እንችላለን ብለዋል።