ትልቅ ፀጋ የተቸረው የሶፍ ዑመር እና የባሌ አካባቢ የመልማት ዕድል ተነፍጎ መቆየቱ ያስቆጫል - ኢዜአ አማርኛ
ትልቅ ፀጋ የተቸረው የሶፍ ዑመር እና የባሌ አካባቢ የመልማት ዕድል ተነፍጎ መቆየቱ ያስቆጫል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2018 (ኢዜአ)፡- ተፈጥሮ አብዝቶ በረከት የቸረው የባሌ ተራሮች እና ሶፍ ዑመር አካባቢ በሚፈለገው ልክ ሳይለማ መቆየቱ እንዳስቆጫቸው የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀድሞና በሥራ ላይ ካሉ አመራሮች ጋር በሶፍ ዑመር ቆይታ አድርገዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ በዚሁ ወቅት፤ ሁለቱ ባሌዎች አንድ ላይ ሆነው የኢትዮጵያን 3 ነጥብ 9 የቆዳ ስፋት እንዳላቸው አንስተዋል።
ይህን ያህል የሀገሪቱ ክፍል ከልማት ተነጥሎ የልማት እንቅስቃሴ ያልነበረበትን ወቅት ሳስብ አዝናለሁ ብለዋል።
አሁን ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ እና በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተሠሩ በርካታ ሥራዎች ከገመትኩት በላይ አበረታች ናቸው፤ለአብነትም በሁለቱ ባሌዎች 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት መታረሱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
በቱሪዝሙም ተደብቆ የኖረው ፀጋ ያስቆጫል ያሉት አማካሪው፤በሁለቱ ዞኖች ከ360 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ ለዱር አራዊት መመደብ መቻሉ ትልቅ ደግነት መሆኑን አመላክተዋል።
የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች ናቸው፤ዞኑ ካለው ጸጋ አንጻር ግን በቀጣይ ብዙ መሥራት ይጠይቃል ሲሉም ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ከሶፍ ዑመር አጠገብ ሆኜ ሶፍ ዑመርን የማየት ፍላጎቱ አልነበረኝም፤ ብፈልግም መሠረተ ልማት አልተሟላለትም ነበር ብለዋል።
አሁን ከ13 ዓመታት በኋላ ወደ ስፍራው በመምጣት ሶፍ ዑመር መልክ-ዓምድር ብቻ ሳይሆን ታሪክ መሆኑን ለማየት በመብቃቴ ደስ ብሎኛል ሲሉም ተናግረዋል።
በባሌ እና ሶፍ ዑመር ያለውን ታሪክ ብሎም አቅም መጠቀም የሚያስችል ዕይታ ቀደም ሲል አለመኖሩ ግን ያስቆጫል፤ በእርግጥ አሁን ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለዋል።
በመሆኑም ልማቶቻችን እና የቱሪዝም መስኅቦቻችን ሰላማችንን የምናረጋግጥባቸው፤ ሰላማችንን በማረጋገጣችን ምክንያትም ሌሎች ተጨማሪ አጋጣሚዎችን ምንገነባባቸው እንዲሆኑ ሁላችንም መሥራት አለብን ነው ያሉት።
ወደ አካባቢው በመምጣታቸው በአንድ በኩል ቁጭት፤በሌላ መንገድ ተስፋ፤ ለምን ድሃ ሆንን? መርጠን ነው ወይስ? የሚል ቁጭት አዘል ጥያቄ አጭሮብኛል ያሉት ደግሞ የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ናቸው።
በአጭር ጊዜ የተሠራው ሥራ ደርዘ ብዙ መሆኑ ገጠሩንም ከተማውንም ከጫፍ ጫፍ ለማዳረስ እየተደረገ ያለው ርብርብ የልጆቻችን ኢትዮጵያ ምን ያህል ተገቢውን ስፍራ እየያዘች እንደሆነ አስረጂ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
ባሌ ላይ ሀገርንና ሕዝብን አውቆ በጥበብ የመምራት ትምህርት ወስጃለሁ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ የት ቦታ ምን ሀብት አላት? ምን ቅርስ አላት? ብሎ አውቆ አመራር ሰጥቶ በቅርብ ተከታትሎ መምራትን ተምሬያለሁ ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ፀጋን አውቆ መምራት እና የፖለቲካ ባህል ለውጥ ላይ እየተሠራ ያለው ተግባር የሥራ ውጤት መሆኑን ከባሌና ሶፍ ዑመር ቆይታቸው መገንዘባቸውን አንስተዋል።