ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አበክሮ ሊሰራ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ):- የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትጋት፣ ልፋት እና ድካም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ‘የሶፍ ኡመር ወግ’ ከቀድሞ እና በሥራ ላይ ካሉ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀገር በአንድ ትውልድ አይሰራም አንድ ትውልድ ጀምሮ የሚጨርሰው ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

በየትኛውም ዓለም ያለ ሀገር የሚሰራው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትውልዶች የትናንት ማንነታቸው፣ የዛሬ መኖራቸው እና የነገ መጻኢ ጊዜ የጋራ ውጤቶች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።


 

የትውልድን የተሟላ ማንነት በውል መረዳት ሀገር የመገንባት ብቃት እና እሳቤን እንደሚያሰፋም ነው የተናገሩት።

በዚህ የትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ሀገር ትገነባለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም በሚኖርበት ዘመን ውስጥ ለሀገሩ መልካም ከመመኘት ባለፈ መልፋት፣ መድከም እና መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

ያለ ድካም እና ልፋት ሰላም እና ብልጽግና አይመጣም፤ ፍሬም ሊታይ አይችልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የምናልመውን ብልጽግና ለማምጣት በላቀ ትጋት ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም