ጠቅላይ ምክር ቤቱ የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ስርዓተ ቀብር ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ እንዲፈፀም ለአደረጉ አካላት ምስጋና አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ምክር ቤቱ የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ስርዓተ ቀብር ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ እንዲፈፀም ለአደረጉ አካላት ምስጋና አቀረበ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ስርዓተ ቀብር ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ እንዲፈፀም ለአደረጉ ሁሉም አካላት ምስጋና አቅርቧል።
ታላቁ ዐሊም ካረፉበት ጊዜ አንስቶ የሽኝት ሥነ-ሥርዓቱ እና ሌሎች ተያያዥ መርሐ ግብሮች የበርካቶች አባት የሆኑትን ዐሊም ክብር እና እስላማዊ አደብ ተጠብቆ እንዲከናወን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትንም ጠቅላይ ምክር ቤቱ አመስግኗል።
በተለይም ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት፣ ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለሰላም ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ለሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ለኦሮሚያ ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባና ለፌዴራል ትራፊክ ፖሊስ፣ ለደንብ ማስከበር፣ ለቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴዎች፣ ለኑር መስጂድ እና ለአንዋር መስጂድ ወጣቶች፣ ለመንግሥት እና ለግል መገናኛ ብዙኃን፣ ለመላው የከተማው ነዋሪዎች ሁሉ የታላቁ ዐሊም ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ትልቅ ክብር እንዳለው ገልጾ ምስጋናውን አቅርቧል።
ታላቁ ዐሊም የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባት እንደመሆናቸው፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላሳየው ፍቅርና ክብር ጠቅላይ ምክር ቤቱ ትልቅ ክብር እንደሚሰጥ ማስታወቁን ኢቢሲ ዘግቧል።
የሃይማኖት ተቋማትም ሕዝበ ሙስሊሙ ተወዳጁን አባት እና ዐሊም በአጣበት ወቅት ከጎኑ በመቆም ሀዘኑን ለመካፈል ያደረጉት ሁሉ ታሪክ የማይረሳው ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ታላቁ ዐሊም ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስን አሏህ ምንዳቸውን ጀነተል ፊርደውስ ያድርገው፣ ምህረቱንም ይለግሳቸው ሲል ምኞቱን ገልጾ፣ ለመላው ቤተሰብና ወዳጆቻቸውም መጽናናትን ተመኝቷል።