የሮክፌለር ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሮክፌለር ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018 (ኢዜአ):- የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅት ሮክፌለር ፋውንዴሽን የኢኮኖሚ ዘርፉን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅት ሮክፌለር ፋውንዴሽን የአፍሪካ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ኢሲኮ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሩ ሮክፌለር ፋውንዴሽን በዓለም ደረጃ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና የልማት ኢኒሼቲቮችን ለመደገፍ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ከፋውንዴሽኑ የቅድሚያ የትኩረት መስኮች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸው የልማት ዕቅዱን ግቦች ለማሳካት በቂ፣ የረጅም ጊዜና ተመጣጣኝ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር፣ የፋይናንስ ቀውሶችን የመቋቋም አቅም መገንባትና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ኢኒሼቲቮችን ትግበራ ማሳደግን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ፋውንዴሽኑ ሊሰሩባቸው የሚችሉ ቁልፍ መስኮችን አንስተዋል።
የሮክፌለር ፋውንዴሽን የአፍሪካ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ኢሲኮ ፋውንዴሽኑ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው ሀገሪቱ በፋውንዴሽኑ የፋይናንስ ፕሮግራም ላይ እንደምትካተት ጠቁመዋል።
“አክስለሬሽን ፕሮግራም” የተሰኘው መርሃ ግብር ሀገራት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) የኢኮኖሚ አይበገሬነት እና ዘላቂነት ኢኒሼቲቭን የመሰሉ የፋይናንስ አማራጮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያገኙበት ማዕቀፍ ነው።
ሁለቱ ወገኖች የመንግስትን የፖሊሲ ሪፎርም ከግሉ ዘርፍ ኢኖቬሽን ጋር በማስተሳሰር በዘላቂ ግብርና፣ ታዳሽ ኃይል እና ዳታ መር የልማት እቅድ ላይ አጋርነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።