ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካውያን የመቻል ምልክት እና ቀጣናዊ ትስስር መፍጠሪያ የትውልድ አሻራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካውያን የመቻል ምልክት እና ቀጣናዊ ትስስር መፍጠሪያ የትውልድ አሻራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካውያን የመቻል ምልክት፣ ቀጣናዊ ትስስር መፍጠሪያ የትውልድ አሻራ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ እና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የጽሕፈት ቤት የስራ ኃላፊዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት፤ የመላ ኢትዮጵያውያን የላብ የደምና የእንባ ጠብታ ያረፈበት የሕዳሴ ግድብ ድንቅ የመቻል ትዕምርት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው፣ ገንዘባቸውን አውጥተው በራሳቸው እውቀት የገነቡት የመላ አፍሪካውያን ዳግማዊ ዓድዋ ነው ብለዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትርጉሙ የላቀ ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ ኢትዮጵያውያን ለትውልድ አሻራቸውን የጣሉበት የድል ሀውልት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚ አካሉ በአግባቡ እንዲያስፈጽም በሕግና መመሪያ ሲደግፍና ሲቆጣጠር መቆየቱን በመጥቀስ፤ በዚህም ተፈጥሮ የቸረችንን ሀብት መጠቀም የምንችልበትን ዕድል ፈጥረናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ መግለጿን አስታውሰው፤ የግድቡ መጠናቀቅ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትብብር የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ጀምራ የማትጨርሰው ፕሮጀክት እንደሌለ የሚያሳይ የመቻል ምልክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የብዙዎች ጥያቄ "ለምን ተሰራ ሳይሆን እንዴት ቻሉት" የሚል መሆኑን በመግለጽ፤ አፍሪካ እንደምትችል ኢትዮጵያ ትልቋ ማሳያ ናት ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመተባበራችን ውጤት ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካም ትሩፋት ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል ከማመንጨት ባለፈ ለፖለቲካና ደህንነት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ምቹ ሥነ ምህዳር የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እንዲያገለግል የሚያስችል መሆኑን በማነሳት፤ ለዚህ ደግሞ አስፈላጊው መሰረተ ልማት እንዲሟላ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረዳት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ሀይሌ፤ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፍላጎቷን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሲጠነሰስ የነበራት በጋራ የመልማት ፍላጎት ከተጠናቀቀ በኋላም አቋሟ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ከግድቡ የሚመነጨው ሀይል ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የዲፕሎማሲያችን ውጤት ነው ያሉት የረዳት የመንግሥት ተጠሪዋ፤ የኢትዮጵያ በጋራ የመበልጸግ ፍላጎት አፍሪካን የሚቀይር ኢኒሼቲቭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፤ ግድቡ የኢትዮጵያውያን የትብብራቸው ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዓለም ላይ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች በስኬት የሚጠናቀቁት በህዝብና መንግስት ትብብር መሆኑን በማንሳት፤ የመንግስት አመራር ሰጭነትና የህዝቡ ቁርጠኝነት ለውጤት አብቅቶታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድብ ያወጣነው ገንዘብ የት ደረሰ የፈሰሰው ላባችን ከምን ደረሰ የሚለውን ለማረጋገጥ የሕዳሴ ግድብን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ከሀይል ማመንጫነት ባለፈ ትልቅ የቱሪዝም ማዕከል እንደሚሆን ገልጸው፤ ባለሃብቶች በግድቡ ዙሪያ ባለው ልማት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡