ቀጥታ፡

የሰላም ቀንዲል የሆኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን መልካም አርዓያ ነበሩ - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦የሰላም ቀንዲል የሆኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን መልካም አርዓያ እንደነበሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የአስክሬን ሽኝት በሚሊኒዬም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

ከአስክሬን ሽኝት መርሃግብሩን ተከትሎ  ሥርዓተ ቀብራቸው  የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ኡለማዎች፣ ደረሳዎች፣ ኡስታዞች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል።


 

የአስክሬን ሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፤ኢትዮጵያ ዛሬ መልካም መምህርና የሁሉም ኢትዮጵያዊ አባት የሆኑትን ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስን በማጣቷ መሪር የሐዘን ቀን ሆኗል ብለዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሁሌም ሲታወሱ የሚኖሩ እንቁ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ መልካም አበርክቷቸው በተለየ ሁኔታ የሚነገርላቸው ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትና መላው ኢትዮጵያዊ በሐጂ ሕልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፣ ለመላው ቤተሰብና ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን ይመኛል ብለዋል።

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ በጎነት፣ጥበብና አርአያነት በሁላችንም ዘንድ ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤መልካም አርዓያነታቸውን መከተል ለእርሳቸው የምንሰጠው ትልቁ ክብር እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራር በነበሩበት ወቅት የህዝቦች አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር በከፍተኛ ደረጃ ሰርተዋል ብለዋል።


 

በአመራር ዘመናቸው የእስልምና እምነት ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በቅንነት ያገለገሉ ታላቅ አባት ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

በተለይም ለሰላም፣ለአብሮነትና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ እንደነበርም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህ በጎ ተግባራቸው ሁል ጊዜ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚዘከርና የሚታወስ መሆኑን ጠቁመው፥ ለቤተሰባቸው፣ለእምነቱ ተከታዮችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሽኝት መርሃ ግብሩ ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ህልፈት ለመላው ኢትዮጵያውያን እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው ብለዋል፡፡


 

እድሜያቸውን ሙሉ ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት መጠናከር የሰጡ የመላው ኢትዮጵያውያን አባት እንደነበሩም ነው የተናገሩት፡፡

ይህ መልካምነት  እና ደግነታቸው ሁሌም ከእኛ ጋር አብሮ ይኖራል ነው ያሉት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመልዕክታቸው፡፡ 

የመልካምነት አሻራቸው ለትውልድ እንዲተላለፍ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም