የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የማድረግ ጥረት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የማድረግ ጥረት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የማድረግ ጥረት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ተናገሩ።
የፍትህ ተርጓሚዎች አመታዊ ጉባኤ በድሬዳዋ አስተዳደር ተካሂዷል።
በመድረኩ በፌዴራል እና በክልል ፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ አፈጻጸም ወቅት የታዩ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች፣ የዳኝነት አገልግሎትን ዲጂታላይዝ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፤ የፍትህ አገልግሎት ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን የማረጋገጥ ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊና ቀልጣፋ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች፣ የድሬዳዋ እና የአዲስአበባ ከተማ መስተዳድሮች ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች እየገነቡ ያሉት ወረቀት አልባ የፍትህ አገልግሎትንም (ኢ-ኮርት) እስከ ቀበሌ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመድርኩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ፤ የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በመደገፍ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉንም ገልጸዋል።