በአፍሪካ በአምስት ሀገራት የሴቶች የግብርና ስራዎችን መደገፍ የሚያስችል መርሃ ግብር ተግባራዊ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ በአምስት ሀገራት የሴቶች የግብርና ስራዎችን መደገፍ የሚያስችል መርሃ ግብር ተግባራዊ ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦በአፍሪካ በአምስት ሀገራት የሴቶች የግብርና ስራዎችን መደገፍ የሚያስችል መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉ ተገለጸ።
የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል፣ የዓለም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዘዴ፣ ቅኝትና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ(ኤዩዲኤ-ኔፓድ) ስልጠና ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮግራም ኦፊሰር ኤድና ካሊማ እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችሉ፣ የምግብ ዋስትና ሽግግርን ለመፍጠር የሚረዱ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
በኢትዮጵያ፣ ማላዊ፣ ሩዋንዳ፣ ኒጀርና ካሜሩን በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ የሴቶች የግብርና ሥራዎችን የሚደግፍ መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፤ ይህንን በሌሎች አገራት ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፈር ለምነትና ጤንነት፣ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አስተዳደር፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በአለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዘዴ፣ ቅኝትና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ጥምረት ተመራማሪ ኒኮል ሀራሪ፤ ጥምረቱ በኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በፊት የተጀመረ ጥምረት መሆኑን ገልጸዋል።
ጥምረቱ ዘላቂ የሆነ የአካባቢ ጥበቃና አስተዳደር ላይ የእውቀት ሽግግር መፍጠር ላይ የሚሰራ ኤክስፐርቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎች ባለሙያዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት የተዘጋጀው ስልጠናም ከ30 በላይ አገራት የተውጣጡ ከመንግስት፣ ምሁራን፣ የግል ዘርፍና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩም ዘላቂነት ያለው የመሬት አስተዳደር ስርዓት የኢትዮጵያ ተሞክሮ ይቀርባል ብለዋል።
የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዳይሬክተር ጀነራል ጌቴ ዘለቀ ( ዶ/ር)፥ ማዕከሉ ምርምር ላይ መሰረት ያደረጉ የውሃና የተቀናጀ መሬት አያያዝ፣ አየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከመንግስትና አጋራት ጋር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት የተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ደረጃ የሚገኙ መልካም ተሞክሮዎችን የመቀመርና የማስፋት ሥራ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚያከናውን ተናግረዋል።