ቀጥታ፡

ባህር ዳር ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ድል ቀንቷቸዋል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10 /2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር  ባህር ዳር ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸንፍ ዓመቱን በድል ጀምረዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 3 ለ 1 አሸንፏል። 

ክንዱ ባየልኝ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ሳቲ ኦሴ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ጫላ ተሺታ ለሀድያ ሆሳዕና ብቸኛዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

የሀድያ ሆሳዕናው ኤልያስ መሐመድ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። 


 

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጨዋታ ምድረ ገነት ሽሬ በዳንኤል ዳርጌ ግብ መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 አሸንፏል። 


 

አስቀድሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ውጤቶቹን ተከትሎ የአንደኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል። የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም