ቀጥታ፡

በደሴ ከተማ የ2018 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምገባ  ፕሮግራም ተጀመረ 

ደሴ ፤ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ አስተዳደር የ2018 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተጀመረ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ፕሮግራሙን ባስጀመሩበት ስነ ስርአት ላይ እንደገለጹት ከከተማ አስተዳደሩ በጀት በተጨማሪ ባለሃብቶችን፣ ድርጅቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም ዛሬ ተጀምሯል።


 

የምገባ ፕሮግራሙ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ፣ የትምህርት አቀባበላቸውን ለማሳደግና ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በትምህርት ዘመኑ ከምገባ ፕሮግራሙ ጎን ለጎን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅር አበበ በበኩላቸው፣ በትምህርት ዘመኑ በ32 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ23ሺህ በላይ ተማሪዎችን በምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በዛሬው እለትም የምገባ ፕሮግራሙን በስምንት ትምህርት ቤቶች ከ4 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ማስጀመር መቻሉን ተናግረዋል።


 

ባለፉት ሶስት ዓመታት በተካሄደ የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት  እንዲከታተሉና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የሮቢት 1ኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መሀመድ ይማም ናቸው።

በማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ላይ  የከተማው አመራር አካላትና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም