ቀጥታ፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ የሰላም እና የአብሮነት አባት ነበሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ የሰላምና የአብሮነት አባት ነበሩ ሲሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለ40 ዓመታት ባስተማሩበት ኑር መስጂድ አስክሬን ሽኝት ተደርጎላቸዋል።


 

በዚሁ ጊዜ አስተያየታቸውን የሰጡ እስልምና እምነት ተከታዮች ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ በሕይወት ዘመናቸው ስለ ሰላምና አብሮነት በትኩረት ያስተማሩ አባት ናቸው ብለዋል።

አምባሳደር ሀሰን ታጁ እንደተናገሩት፤ የተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ሐዘንን የፈጠረ ክስተት ነው። 


 

በህይወት ዘመናቸው የሀገር አንድነት እና አብሮነት ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን ያስተማሩ አባት እንደነበሩ ተናግረዋል።

በሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነትን ያገኙ የሰላም እና የእርቅ አባት ነበሩ ሲሉም ገልፀዋል።

ሼህ አብዱልሃሚድ አህመድ በበኩላቸው የእርሳቸው መልዕክቶች ሁሌም የኢትዮጵያዊነትን እሴት፣ የሃይማኖቶች መከባበርን እና የወንድማማችነት መንፈስን የሚያጎሉ ነበር ብለዋል።


 

የሀገርን ሰላም እና አንድነት በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አክለው ገልፀዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ የሀገር አለኝታና ዋርካ ነበሩ ሲሉ የገለፁት ደግሞ  የአንዋር መስጅድ አሰጋጅ ያሲን ሰልማን ናቸው።


 

በተገኙበት ሁሉ ስለ ሰላም፣ አንድነት እና አብሮነት ሲያስተምሩ እንደኖሩ ገልጸው፥ ትውልዱም ይህን አርዓያ በመከተል ለሀገር ሰላም እና አንድነት መሥራት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም