ቀጥታ፡

የወልቂጤ ከተማ የኮሪደር ልማት ዘመናዊና ምቹ በሆነች ከተማ ለመኖር አስችሎናል- ነዋሪዎች

ወልቂጤ ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ የወልቂጤ ከተማ የኮሪደር ልማት ዘመናዊና ምቹ በሆነች ከተማ ለመኖር አስችሎናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት በከተሞችና በገጠር ጭምር ተግባራዊ እየተደረገ አስደናቂ ለውጥ እየታየበት መሆኑ ይታወቃል።

ከአዲስ አበባ የጀመረው የከተሞች ኮሪደር በክልሎችም እየተስፋፋ መጥቶ ከተሞች የተዋቡና ለመኖሪያ ምቹ እንዲሁም ዘመናዊ እንዲሆኑ እያስቻለ ይገኛል።


 

የልማት ስራው ተጠቃሚ ከሆኑ ከተሞች መካከል ወልቂጤ ተጠቃሽ ስትሆን ነዋሪዎቿም ለተከናወነው ስራ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና በየደረጃው ያሉ አመራሮችን አመስግነዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በከተማዋ ተዘዋውሮ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙሰማ በሽር፣ አቶ ፉአድ አብደላ እና አቶ ደበበ ስባኒ፤ የወልቂጤ ከተማ የኮሪደር ልማት ዘመናዊና ምቹ በሆነች ከተማ ለመኖር አስችሎናል ብለዋል።


 

የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገዶችን በመገንባት የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነትን የቀነሰ መሆኑን እንዲሁም ለከተማዋ የንግድ ስራ መነቃቃት፣ ለመዝናኛ እና ለኑሮ ጭምር ተመራጭ እንድትሆን አስችሏታል ሲሉም ተናግረዋል።


 

በየደረጃው ያለው የዞንና የከተማዋ አመራሮች፣ አጠቃላይ ማህበረሰቡና ባለሃብቶች የነቃ ትብብርና ተሳትፎ ታክሎበት ልማቱ የተሳካ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ይሄው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙራድ ከድር፤ በከተማዋ እስካሁን 17 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በልማቱ አካል ጉዳተኞችን ጭምር ታሳቢ ያደረገ የእግረኛ መንገድ፣ የብስክሌትና የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ የአረንጓዴ ስፍራዎችና መዝናኛዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም የከተማዋ ውበትና ለኑሮ ምቹነት እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተው የልማት ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ የልማት ስራ አጠቃላይ ነዋሪው፣ ባለሃብቶችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብርና ተሳትፎ አስደናቂ መሆኑን ገልጸው ለሁለተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማትም ይሄው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም