በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ መድረኮችን በብቃት ማስተናገድ የሚያስችል የተቀናጀ አቅም ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ መድረኮችን በብቃት ማስተናገድ የሚያስችል የተቀናጀ አቅም ተገንብቷል

ባሕርዳር፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፡- በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ መድረኮችን በብቃት ማስተናገድ የሚያስችል የተቀናጀ አቅም መገንባቱን የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
"አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሚካሄደው 11ኛው ጣና ፎረም የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ የጸጥታ አካላት የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ መድረኮችን በብቃት ማስተናገድ የሚያስችል የተቀናጀ አቅም መገንባቱን ገልጸዋል።
የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የጸጥታ ሃይሉ የላቀ ሚና እንዳለ ሆኖ የህዝቡ ትብብርና ጥረት ከፍተኛ አቅም መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ ባህር ዳርን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አረጋግጠው በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ከቀናት በኋላ ለሚካሄደው ጣና ፎረም በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የቢሮው ኃላፊ አረጋግጠዋል።
የጣና ፎረምን የኢትዮጵያን ከፍታ ብሎም የክልሉን ገፅታ በሚያሳይ መልኩ ተቀብሎ በማስተናገድ መልካም እሴቶችንና እንግዳ ተቀባይነትን ማሳየት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)፤ የፖሊስ ተቋሙን መልሶ በማደራጀት ባለፉት ወራት በርካታ ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
ለጣና ፎረም የተሟላና የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ለፎረሙ ስኬታማነት የፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መግባቱን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ በፀጥታ ግብረ ሃይሉ የተካተቱ የክልሉና የፌደራል የፀጥታ አካላትና በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።