ቀጥታ፡

በህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንዲያገኙ ድጋፍ እና ቁጥጥር ይጠናከራል

አሶሳ፤ ጥቅምት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንዲያገኙ ድጋፍ እና ቁጥጥር ይጠናከራል ሲሉ የክልሉ  ምክርቤት አፈ-ጉባኤ አስካለች አልቦሮ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክልሉ ተመራጮች በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ያከናወኑትን የህዝብ የውይይት መድረክ አስመልክቶ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ምክክር አድርገዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስካለች አልቦሮ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና ሌሎች ትልልቅ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።

ክልሉ በራሱ አቅም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረው ለስኬታማነቱም ምክር ቤቶች ሚናቸውን ያጠናክራሉ ብለዋል።

የተቋማት ተደራሽነት እና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በህብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እንዲመለሱ ድጋፍ እና ቁጥጥሩ የሚጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የክልሉ ተመራጭ አቶ ሙባረክ ኤሊያስ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሰፈነው ሠላም የተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረጉን በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።

በህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚነሳው የትራንስፖርት ችግር እና ሌሎች ተያያዠ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ቁጥጥር እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም