ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት የተጉ የመላው ኢትዮጵያውያን አባት ነበሩ - ኢዜአ አማርኛ
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት የተጉ የመላው ኢትዮጵያውያን አባት ነበሩ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት የተጉ የመላው ኢትዮጵያውያን አባት ነበሩ ሲሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ፡፡
የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስክሬን የሽኝት መርሃ ግብር በሚሊኒዬም አዳራሽ ተካሂዷል።
በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሽኝት መርሃ ግብሩ ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ማለፍ ለመላው ኢትዮጵያውያን እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው ብለዋል፡፡
ሰውነትን ከዘርና ከሃይማኖት ያስበለጡ በሁሉም ዘንድ የሚወደዱ እና በንግግር ለዛቸው ለሁሉም አርአያ የሆኑ አባት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
እድሜያቸውን ሙሉ ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት መጠናከር የሰጡ የመላው ኢትዮጵያውያን አባት እንደነበሩ አመላክተዋል፡፡
ይህ መልካምነት እና ደግነታቸው ሁሌም ከእኛ ጋር አብሮ ይኖራል ነው ያሉት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ በመልዕክታቸው፡፡
የመልካምነት አሻራቸው ለትውልድ እንዲተላለፍ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል ብለዋል፡፡