ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚመነጭ የጋራ አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚመነጭ የጋራ አጀንዳ መሆኑ ተገለጸ።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅና በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የሁለቱ የውሃ ሥርዓቶችና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነት፥ የዓባይና የቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልልን ስትራቴጂካዊ ሚና መዳሰስ" በሚል መሪ ሃሳብ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምክክር ተካሂዷል።


 

የአፋር ክልልን ስትራቴጂክ ሚና፣ ከታሪክ ባህልና ወቅታዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ አንጻር የሚዳስስ የመነሻ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የአፋር ክልል የሥራና የከተማ ልማት አማካሪ ኢንጂነር አሊ መሀመድ እንደገለጹት፤ የሀገራችን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊ ነው።

በቀጣይም ኢትዮጵያን ወደ ባሕር በር ባለቤትነት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የአፋር ህዝብ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አመልክተዋል።

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ሬዶ የባህልና ሀገር በቀል እውቀቶች ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር መሀመድ አህመድ፤ ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያውያን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ሁለንተናዊ መስተጋብር ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ዜጎች ማንኛውንም ዓይነት ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ በመደገፍ በትብብር መስራት የሚጠበቅ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአፋር ክልል መንግስት ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉት አቶ መሀመድ አወል፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሴሩ የባንዳና ባዕዳን ኃይሎችን ሸፍጥ በጋራ መመከት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ከሚደግፉ የቀጣናው ሀገራት ህዝቦች ጋር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና የሠመራ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በአካዳሚክ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፣ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሀመድ ዑስማን (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ኮሞዶር ተገኝ ለታ፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም