ቀጥታ፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ታላቅ ምሁር እና በጎ አባት ነበሩ - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ታላቅ ምሁርና በጎ አባት ነበሩ ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ፡፡

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ የአስክሬን ሽኝት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሄዷል፡፡


 

በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በስነ ስርዓቱ ላይ ኢትዮጵያ ዛሬ ታላቅ ምሁር፣ መልካም መምህርና አባት የሆኑትን ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስን በማጣቷ መሪር የሐዘን ቀን ሆኗል ብለዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ በእውቀታቸው፣ በጥበባቸው፣ በእርጋታቸውና በልግስናቸው ሁሌም ሲታወሱ የሚኖሩ እንቁ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ የእውቀት ልግስናቸውና መልካም አበርክቷቸው በተለየ ሁኔታ የሚነገርላቸው ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትና መላው ኢትዮጵያዊ በሐጂ ሕልፈት ጥልቅ ሐዘን የተሰማው መሆኑን በመግለጽ፣ ለመላው ቤተሰብና ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን ይመኛል ብለዋል።

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ በጎነት፣ ጥበብና አርአያነት በሁላችንም ዘንድ ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ መልካም አርዓያነታቸውን መከተል ለእርሳቸው የምንሰጠው ትልቁ ክብር ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም