ቀጥታ፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ  ለሰላም፣ለአብሮነትና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በመላ ኢትዮጵያውያን ሲታወስ ይኖራል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ  ለሰላም፣ለአብሮነትና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በመላ ኢትዮጵያውያን ሲታወስ  ይኖራል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪስ ገለጹ።

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስክሬን የሽኝት መርሃ ግብር በሚሊኒዬም አዳራሽ ተካሂዷል።


 

በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራር በነበሩበት ወቅት የህዝቦች አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር በከፍተኛ ጥረት ሲሰሩ ነበር ብለዋል።


 

በአመራር ዘመናቸው የእስልምና እምነት ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በቅንነት ያገለገሉ ታላቅ አባት ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

በተለይም ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ እንደነበርም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህ በጎ ተግባራቸው ሁል ጊዜ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚዘከርና የሚታወስ መሆኑን ጠቁመው ለቤተሰባቸው፣ ለእምነቱ ተከታዮችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም