ኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ በካፒታል ገበያ ልማት በትብብር ለመስራት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ በካፒታል ገበያ ልማት በትብብር ለመስራት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10 /2018 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ልማት ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከስብሰባው በተጓዳኝ ከአይኤምኤፍ የሞኒተሪ እና የካፒታል ገበያዎች የስራ ክፍል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ መካከል በሞኒተሪ ፖሊሲ፣በካፒታል ገበያዎች እና የፋይናንስ መሰረተ ልማት ጨምሮ በቁልፍ መስኮች ያላቸውን ትብብር እና የቴክኒክ ትስስር ማጠናከርን ያለመ ነው።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ስር የታዩ ለውጦችን ያነሱ ሲሆን ብሄራዊ ባንክ የማይበገር የፋይናንስ ተቋማት አቅም ለመገንባት፣አካታችነትን ለማረጋገጥ እና የፋይናንስ መሰረተ ልማትን ለማዘመን የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አብራርተዋል።
የባንኩ ገዥ እንደ አይኤምኤፍ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና የፖሊሲ ትግበራ አቅም ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ የሚያስችል ጠንካራ አጋርነትን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የገበያ መረጃ፣ የካፒታል ገበያ ልማት እና የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን ማጠናከርን ጨምሮ በጋራ እየተገበሯቸው ያሉ የቴክኒክ ድጋፍ ኢኒሼቲቮችን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ የሞኒተሪ እና ካፒታል ገበያ ሪፎርሞች፣ የፋይናንስ መረጋጋት እና ኢትዮጵያ ከዓለም የፋይናንስ ስርዓት ጋር የበለጠ እንድትተሳሰር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ለመስራት መስማማታቸው ተመልክቷል።