ለጣና ፎረም በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለጣና ፎረም በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል

ባሕርዳር፤ ጥቅምት10/2018(ኢዜአ)፡- ከቀናት በኋላ ለሚካሄደው ጣና ፎረም በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
"አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሚካሄደው 11ኛው ጣና ፎረም የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ የጸጥታ አካላት የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ፤ ከቀናት በኋላ ለሚካሄደው የጣና ፎረም በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በፎረሙ የሚታደሙ እንግዶች ሁሉ ከጉባኤው ተሳትፎም ባለፈ በሚኖራቸው ቆይታ በመልካም መስተንግዶና ጥሩ አቀባበል የማይረሳ ጊዜ እንዲያሳልፉ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የጸጥታ ሃይሉ ሰላምና ደህንነታቸውን በማስጠበቅ፤ የከተማውና የአካባቢው ህዝብ ደግሞ መልካም መስተንግዶ ማድረግ እድሚጠበቅበትም አስታውቀዋል።
በጣና ፎረም ላይ ከተለያዩ አገራት የሚመጡትን ጨምሮ በርካታ ታዳሚዎች የሚገኙ በመሆኑ ከጸጥታም ይሁን ከቀአባበልና መስተንግዶ አንፃር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ መሰራቱንና ዝግጅቱም መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የጣና ፎረም ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተው ጉባኤው የሚካሄድባት ባህር ዳር ከተማ ደግሞ የሰላም ተምሳሌትና የቱሪዝም መስህብነቷን የምታሳይበት መልካም አካጣሚ መሆኑንም አስረድተዋል።
ፎረሙ በመሪዎችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ምክክር የሚደረግበት መርሃ ግብር ያካተተ፤ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ልዩ መልዕክተኞችም የሚወያዩበት መሆኑ መገለጹ ይታወቃል።
በርካታ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀው 11ኛው የጣና ፎረም "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 14 እስከ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕዳር እና በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።