ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን ያጎለብታል - ምሁራን

ሐረማያ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲጎለብት በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያበረክት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የምስራቅ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም ምስረታ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በምክክሩ መድረክ ላይ የተሳተፉት ምሁራን ለኢዜአ እንደተናገሩት የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር የምርምር ቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲጎለብት ፋይዳው የላቀ ነው።


 

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ትስስር አስተባባሪ ፈይሳ ሁንዴሳ እንዳሉት፤ ትስስሩ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲዎችና - ኢንዱስትሪዎች በተበጣጠሰ መንገድ የሚያከናውኑት ስራዎችን ወጥ እንዲሆን የሚያስችል  ነው።

ትስስሩም የዩኒቨርsiቲ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የቀሰሙትን እውቀት በኢንዱስትሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ   የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

ትስስሩ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለመፍታት ከዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና፣ ማማከርና የምርምር ቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲያገኙ ያስችላል ያሉት ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር  እሸቱ መኮንን(ዶ/ር) ናቸው።



በኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና አጋርነት ዳይሬክተር ጥምቀተ ዳኜ(ዶ/ር) በበኩላቸው  የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር ሀገራዊ የልማት እቅዶችን በጋራ ለማሳካት እገዛ ያደርጋል።

እንዲሁም የማህበረሰብ ችግሮችን በቅርበት ለመፍታትና የጋራ ችግሮችን አቅዶ በጋራ ለመቅረፍ ብሎም መፍትሄ ለማምጣት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አክለዋል።

 

ትስስሩ ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር በተግባርና ንድፈ-ሃሳብ የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና ዋና ስራ አስኪያጅ አህመድ ረሺድ ናቸው።

በፎረም ምስረታው የምክክር መድረክ ላይ የሐረማያ፣ ድሬዳዋ፣ ሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ኦዳቡልቱምና ቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲዎች፣ የትምህርት ሞያ ስልጠና ኮሌጆች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ የመንግስት እና የግል ኢንዱስትሪ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም