ቀጥታ፡

ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2018 (ኢዜአ)፦  ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄዷል።
 
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችን የበለጠ በማላቅ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።


 
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዳግማዊት ግርማ እንደተናገሩት ቢሮው ዘላቂ እና ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ የሰው ሃይል ልማት፣ ስልጠና ፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት እና ብድር የማመቻቸት ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
 
በስራ እድልና ራስን በምግብ በመቻል በኩል በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው በዚህም ወጣቶችና ሴቶችን በማሰልጠን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በሥራ ላይ ደህንነትና የሥራ ዋስትናን በተመለከተም በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ያለውን ግንኙነት የተሳለጠ ለማድረግና  የኢንዱስትሪ ሠላምን ለማረጋገጥ የሚረዳ ተግባር መከናወኑን ጠቁመዋል።
 
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢንዱስትሪዎችና ለኢንተርፕራይዞች አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር በማስቻል የስራ ዕድል ፈጠራን ያሳድጋል ብለዋል። 



  
የአዲስ አበባ ዲዛይን እና ግንባታ ስራዎች የቢሮ ኃላፊ አማካሪ አህመድ ሀሰን ቢሮው ባለፉት ሶስት ወራት ወጤታማ ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
 
በሩብ ዓመቱ 138 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረጉን ገልጸዋል።
 
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት ተገንብተው ለታለመላቸው ዓለማ እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።
 
በዚህም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው በቀጣይ የተሻለ ስራ እንሰራለን ብለዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም