በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻችንን እንወጣለን - የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻችንን እንወጣለን - የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች
ቦንጋ፤ ጥቅምት 10/2018(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
"የሴቶች፣ ወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ የምክክር” በሚል ሀሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የውይይቱ ዓላማ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ሂደትና ሁኔታ ግንዛቤ አግኝተው ለቀጣይ የኮሚሽኑ ስራ ምክረ-ሀሳብ እንዲሰጡ ማስቻል መሆኑ ተመላክቷል።
በውይይቱ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ለሀገር የሚበጁ ሀሳቦችን ለኮሚሽኑ በመስጠት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አደም አሊ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በፍትሃዊነት እያሳተፈ መምጣቱ ለሀገራዊ ችግሮች በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ አጋዥ ነው ብልዋል።
ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የተሳተፉበት ውይይት መካሄዱም የምክክሩን ሂደት አካታች ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።
በውይይቱም በንቃት በመሳተፍና ሀሳብ በማዋጣት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።
ሴት አካል ጉዳተኞችን በመወከል በውይይቱ የተሳተፉት ወይዘሮ መስከረም ዘለቀ በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማሳተፉ አካታችነቱን የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።
በውይይቱ በንቃት በመሳተፍ ይበጃሉ ያሏቸውን አጀንዳዎችና ሀሳቦች በማቅረብ ለምክክሩ ኮሚሽን ስራ መሳካትና ለሰላም መስፈን ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
ምክክር የችግሮች መፍቻ ቁልፍ በመሆኑ በመድረኩ ሃሳባቸውን ማቅረባቸውን የገለጹት ደግሞ የሴቶች ተወካይ መምህርት ገነት ከበደ ናቸው
በመድረኩም የሴቶችን ሀገራዊ ልማትና አብሮነት ላይ ያላቸውን ሚና በማስመልከት ሀሳባችውን ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
የቦንጋ ከተማ ወጣቶችን ወክሎ የተሳተፈው ወጣት ናትናኤል በድሩ፣ ወጣቶች የኮሚሽኑን ተግባር በተገቢው ተረድተን ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ የማስተባበር ሚናችንን መወጣት አለብን ብሏል።
ወጣቶች ለኮሚሽኑ አላማ መሳካት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጀንዳ የማሰባሰብና ተወካዮችን በመረጠበት ወቅት ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በንቃት መሳተፋቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ናቸው።
የህብረተሰብ ክፍሎቹ ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ጠቅሰው፣ በቀጣይም ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ሁሉም አካል ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አላማ መሳካት ድጋፍና ተሳትፎውን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
በመድረኩ ከክልሉ የተውጣጡ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች በቡድን በመሆን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።