የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2018(ኢዜአ)፦ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በሩብ ዓመቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
ትናንት የተጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተጠናቋል።
በመድረኩ በሩብ ዓመቱ የታቀዱ እና በ90 ቀናት የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት አፈፃፀም ተገምግሟል።
ከንቲባ አዳነች በመድረኩ ማጠቃለያ እንደገለጹት፤ የክረምቱ ወራት የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥተዋል።
በዚህም ምርትን በብዛት በማስገባት የኑሮ ውድነት ጫናን መቀነስና ገበያ ማረጋጋት መቻሉን አንስተዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተከናወኑ ተግባራት የከተማዋን የደን ሽፋን እያደገ መምጣቱንና ጽዱ አካባቢን በመፍጠር ከክረምት ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል መቻሉንም ገልጸዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በመሰረታዊነት መፍታት የሚችለውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በየክፍለ ከተማው የማስፋት ስራ ይሰራል ብለዋል።
የህዝብ የቅሬታ ምንጭ የነበሩ ተቋማት ላይ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ጭምር ተጨባጭ ውጤት መምጣቱንም አንስተዋል።
በስራ ዕድል ፈጠራ በትምህርትና ጤና አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በዘላቂነት ለማስጠበቅ ህዝቡን ያሳተፉ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።
የስራችን ዋነኛ ማጠንጠኛ የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና እርካታን መጨመር ነው ያሉት ከንቲባዋ አመራሩ የተሰጠውን ተግባር በውጤታማነት ለመፈጸም ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክፍለ ከተሞችና በሴክተሮች የአፈጻጸም ልዩነት መስፋት፣ ብልሹ አሰራርና የተቋም ግንባታ ላይ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችን የበለጠ በማላቅ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ በመግለጽ።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው በከተማዋ ባለፋት ሶስት ወራት በአመራሩ የተቀናጀ ስራ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ይሁንና አንዳንድ ተቋማት ላይ የሚታዩ የቅንጅት ክፍቶችን ለይቶ መፍትሔ እንዲያገኙ መትጋት የአመራሩ ሃላፊነት ነው ብለዋል።
ከተማዋን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ፈጠራና ፍጥነት የታከለባቸው አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ናቸው።
በየደረጃው ያለ አመራር በጊዜ የለኝም መንፈስ መሮጥና ያላሰለሰ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።