ቀጥታ፡

በኃብት ስጦታ አንፃር ስንመለከት ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ ኃብት እንዳላት እናውቃለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2018(ኢዜአ)፦ በኃብት ስጦታ አንፃር ስንመለከት ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ ኃብት እንዳላት እናውቃለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በባሌ ዞን ከተለያዩ አመራሮች ጋር ያደረግነው ጉብኝት የመጨረሻ መዳረሻ አስደማሚው የፊንጫ ሀበራ ፏፏቴ ሆኗል ብለዋል።


 

በግርማ የሚወርደው ፏፏቴ ወደ ሶፍኡመር የዋሻ ሥርዓት የሚደመረውን የወይብ ወንዝ የሚቀላቀል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ የሚገኝበት ይኽ አስደናቂ ከባቢ ድንቅ የአዕዋፍ መገኛና በቅርቡ የዋሻ መስህብ የተገኘበት እንዲሁም የራፉ ውብ የዐለት ደን አቅራብያ የሚገኝ ነው ብለዋል።

በቅርቡ በአካባቢው የሚገነባው ማረፊያ ሲጠናቀቅም ለጎብኝዎች የበለጠ ሳቢ እና ምቹ ይሆናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።


 

ባለፉት ሶስት ቀናት በጉብኝቱ የተሳተፉ የቀድሞ እና በሥራ ላይ ያሉ ኃላፊዎች በጉብኝቱ የተመለከቱት የተፈጥሮ፣ የባሕል እና የሰው ኃብት ከፍ ያለ መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።

የጋራ ሥራችን እነዚህን ኃብቶቻችንን መግለጥ፣ ማሳደግ፣ በኃብቶቹ ላይ በመጨመር ቀጣዩ ትውልድ ችቦውን ተረክቦ እንዲቀጥል መሠረት መጣል ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


 

ኢትዮጵያ በርግጥም የተትረፈረፈ ኃብት ምድር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንሰባሰብ ለማለም እንድፈር የጋራ ነጋችንን በጋራ እንገንባ ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም