ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ልማት ፣ዘላቂ ሰላምና ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ የተያዙ አገራዊ ግቦች እንዲሳኩ ህዝቡን በንቅናቄ የማሳተፍ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ልማት ፣ዘላቂ ሰላምና ዲሞክራሲን  እውን ለማድረግ የተያዙ አገራዊ ግቦች እንዲሳኩ ህዝቡን በንቅናቄ የማሳተፍ ስራዎች  ሊጠናከሩ እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ  ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ  ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት በህዝብ ንቅናቄና የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሂዷል። 


 

በውይይቱ ላይ በዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ምክክር ተደርጓል። 

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ  ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ  በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ ዘርፎች በሩብ ዓመቱ ያከናወኑት ስራ የሚበረታታ ነው።  

የተሻለ አፈጻጸምን ማስቀጠል፤  ክፍተት ያለበትን ለመሙላት ርብርብ ማድረግ ይገባል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ  ወጥ የሆነ አፈጻጸም እንዲኖር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ አቅሙ የተገነባ አመራር እና አባል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው  በዚህ ረገድ የአመራር እና አባላት አቅም ግንባታ ስራዎች በትኩረት ሊከናወን ይገባል ብለዋል። 

ተተኪ አመራር  የማፍራት ጉዳይም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 


 

ሰላም፣ዲሞክራሲና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቃል ያሉት አቶ አደም ፤ ህዝቡን በንቅናቄ በስፋት በማሳተፍ ለግቡ ስኬት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል። 

አገራዊ ልማትና ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ የሰላም ግንባታ ስራው ውጤታማ እንዲሆን መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያም የህዝብን እርካታ የሚጨምሩ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ላይ  ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አመልክተው የመልካም  አስተዳደር ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በአጽንኦት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም