ቀጥታ፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አመርቂ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ዋና ስራ አስፈፃሚዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ በሩብ ዓመቱ የታቀዱ እና የ90 ቀናት ዓበይት ተግባራት የአፈፃፀም ደረጃ እየተገመገመ ይገኛል።

ኢዜአ የሩብ ዓመቱን አፈፃፀም በተመለከተ የለሚ ኩራ፣ የልደታ እና የየካ ክፍለ ከተሞች ዋና ስራ አስፈፃሚዎችን  አነጋግሯል።

ስራ አስፈጻሚዎቹ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ የሩብ ዓመቱ ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል።


 

በሩብ ዓመቱ ዜጋ ተኮር የልማት ስራዎች፣ ገበያን የማረጋጋት እና በስራ ዕድል ፈጠራ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውንም አስረድተዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ተጨባጭ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።


 

በተለይ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ሰው ተኮር በሆኑ ተግባራት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በርካታ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ምቹ ከማድረግ ባሻገር ግብዓቶችን በማሟላት የመማር ማስተማር ተግባራትን የማስጀመር ስራ ውጤታማ እንደነበር አስታውቀዋል።

የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ከዝግጅት ምዕራፍ ባሻገር ውጤታማ መደበኛ ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ኃይሌ ናቸው።


 

በተለይም በመልካም አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ የዜጎችን ፍላጎት በማሟላት ረገድ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም