ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእዳ ጫና እና  ንብረት ለውጥ ስጋት ላለባቸው ሀገራት የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ መጠን ሊያሳድግ ይገባል- የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእዳ ጫና እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ የበለጠ እንዲያጠናክር የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ጥሪ አቀረቡ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል። 

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከዓመታዊ ስብስባው ጎን ለጎን ለአየር ንብረት ተጋላጭ የሆኑ የ20 ሀገራት ጥምረት (V20) የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፏል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆነች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ድርቅ፣ ጎርፍ እና የእዳ ጫና የልማት ጉዞዋን እየፈተነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም፣ የታዳሽ ኃይል በማስፋት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስተዋወቅ ለአረንጓዴ እድገት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች ብለዋል።

ሚኒስትሩ ዓለም አቀፉ ማህረሰብ የእዳ ጫና ለበረታባቸው እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ላለባቸው ሀገራት ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

አነስተኛ ወለድ ያላቸው እና በረጅም ጊዜ የሚከፈል የብድር እና ፋይናንስ አቅርቦት ማስፋት፣ የአየር ንብረት የፋይናንስ ድጋፍን ማጠናከር እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምላሾች  የእዳ ሽግሽግን የማድረግ አሰራርን መከተል መንግስታት ለእዳ ለመመለስ የሚከፍሉትን ገንዘብ አየር ንብረት ለውጥን መከላከል ጨምሮ ለሌሎች የትኩረት መስኮች እንዲያውሉ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አጋሮች ጋር በመሆን ፍትሃዊ እና የማይበገር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት ዝግጁ እንደሆነች መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም