ቀጥታ፡

በደርቢው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አጥቂው አቤል ያለው በ66ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

ጋናዊው የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ኢብራሂም ዳንላድ በአቤል ያለው ላይ በሰራው ጥፋት በ53ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ኢትዮጵያ ቡና የተወሰደበት የቁጥር ብልጫ በጨዋታው ላይ ልዩነት የፈጠረበት አጋጣሚ ነበር።

በሁለቱ ቡድኖች የ51ኛው የሊግ የደርቢ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከ17 ሺህ በላይ ደጋፊ በስታዲየም በመገኘት የተከታተለውን ጨዋታ ደጋፊው ድምቀት ሰጥቶታል።


 

በተመሳሳይ ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በረከት ግዛው ለፋሲል ከነማ፣ ዘላለም አባተ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቻል ከወላይታ ድቻ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም