ቀጥታ፡

በምክክር ሂደቱ የታየው ተሳትፎ መጠናከር አለበት-ኮሚሽኑ

ቦንጋ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲጎለብት በምክክር ሂደቱ የታየው ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመለከተ።

ኮሚሽኑ “የሴቶች፣ ወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር” በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄደው የውይይት መድረክ ተጠናቋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ እንደገለጹት ለሁለት ቀናት ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍ በተካሄደው ውይይት ጠቃሚ ሀሳቦች ተነስተዋል።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በኮሚሽኑና በመንግስት መፈፀም ያለባቸው ጉዳዮችን በሰፊው አንስተው ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል ብለዋል።

አጀንዳ መቅርፅና ምክክሩን መምራት የሚችሉ ገለልተኛና ነፃ የሆኑ አወያዮችን መምረጥ የኮሚሽኑ የቀጣይ ተግባር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር የመፍታት ባህል እንዲጎለብት ሁሉም በምክክር ሂደቱ የሚያደርገውን የነቃ ተሳትፎ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች አጋር አካላት ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካልጉዳተኛ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም