ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ጤናማ የንግድ ሥርዓትን በመፍጠር የዋጋ ንረትን የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል 

ሀዋሳ ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ጤናማ የንግድ ሥርዓት በመፍጠር የኑሮ ውድነት ጫናን የሚያቃልሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላከተ፡፡

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሕገ ወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድና፣ የገበያ ንረት መከላከል የጋራ ግብረ ኃይል የንቅናቄ መድረክ አካሄዷል፡፡


 

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ በየነ በራሳ በክልሉ ጤናማ የንግድ ሥርዓትን በመፍጠር የኑሮ ውድነት ጫናን የማቃለል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የምርቶች ነፃ ዝውውር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ የሚገኙ ያልተፈቀዱ ኬላዎች የሚነሱ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ለዚሁ ተግባር የተቋቋመው ግብረ ኃይልም በዚህ ረገድ ተቀናጅቶ በመስራት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የክልልና የፌዴራል ተቋማትን በቅንጅት ያቀፈው ግብረ ኃይሉ ባለፈው ዓመት ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችንና የኮንትሮባንድ ንግድን የመከላከል ስራ ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት መኩሪያ ናቸው ፡፡


 

ቢሮው ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን ሀዋሳ ቅርንጫፍ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው የመከላከል ሥራ ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት የያዘ ሲሆን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እጃቸው ያለባቸውን አካላት በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ መስራቱን አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በተለይ የነዳጅ ግብይቱን ሕጋዊነት ለመጠበቅ ብሎም በዕጥረት ምክንያት በህብረተሰቡ ላይ የሚከሰቱ ጫናዎችን ለማቃለል በየደረጃው በተቀናጀ መንገድ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል፡፡

ከነዳጅ ሕገወጥ ዝውውርና ንግድ ጋር በተያያዘ በ11 ማደያዎችና በ14 ሕገወጥ ነዳጅ ቸርቻሪዎች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመው ከ70 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በሕገወጥ መልኩ ሲዘዋወር መያዙን ገልፀዋል፡፡

በቡና፣ በሸቀጦችና በሌሎች ምርቶች ላይም እንዲሁ ጠንካራ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለፁት ኃላፊዋ ያለፈው ዓመት ጉድለቶቻችንን በመገምገም በተያዘው በጀት ዓመት ይበልጥ የተጠናከረ የጋራ ሥራ እንሰራለን ብለዋል ፡፡

ባለፈው ዓመት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተን በመስራታችን ውጤት ማምጣት ብንችልም ከችግሩ ስፋት አኳያ ብዙ ልንሰራቸው የሚገቡ ሥራዎች አሉ ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋዬ ዴቢሶ ናቸው፡፡


 

ህብረተሰቡ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከልና ለሕግ መከበር እየሰጠ ያለው ቀና ምላሽ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው በተለይ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ወንጀሎችን ህዝቡን በማሳተፍ በትኩረት ልንከላከላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልልና የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ አካላት እንዲሁም የዞን፣ የከተማ አስተዳደርና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም