በክልሉ በተቋማት መልሶ ግንባታ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተቋማት መልሶ ግንባታ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ተችሏል

ኮምቦልቻ ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በተለያዩ ዘርፎች መልሰው እንዲቋቋሙ በተደረጉ ተቋማት ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት መቻሉን የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚያከናውነውን የመልሶ ማቋቋም ተግባር በኮምቦልቻ ከተማ ገምግሟል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን እንደገለጹት፣ በክልሉ በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትን በተሻለ ሁኔታ መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ነው።
በክልሉ በጀት፣ በተለያዩ የልማት ድርጅቶችና አጋር አካላት ትብብር የመልሶ ማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም በርካታ የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃ፣ የግብርና፣ አስተዳደርና ሌሎችም ማህበራዊ ተቋማት በተሻለ ደረጃ መልሰው ተገንብተውና ተቋቁመው የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የመልሶ ማደራጀት ስራው በሰላም እሴት ግንባታ እንዲሁም በሥራ እድል ፈጠራና ሌሎች ዘርፎችንም ውጤታማ ለማድረግ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን በማስቀጠል ተቋማትን መጠበቅና ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ገንዘብ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱ ሙሄ በበኩላቸው፣ በተለያየ ምክንያት የተጎዱ የውሃ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎችም ተቋማትን በተሻለ ሁኔታ መልሶ በማቋቋም ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም በርካታ የመሰረተ ልማት ተቋማት በአዲስ መልክ ተገንብተው ጭምር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ሽዋ ዞን የቀወት ወረዳ ገንዘብ ጽህፈት ቤት የፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ጌታቸው በዞኑ በተለያየ ምክንያት የተጎዱ ተቋማት በተሻለ ደረጃ ተገንብተው ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የፃግብጂ ወረዳ ገንዘብ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ንጉስ ሙሉጌታ በበኩላቸው የተለያዩ ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል ሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ማግኘት ችሏል ብለዋል።
በግምገማ መድረኩ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።