የአርባ ምንጭ የዓዞ እርባታን ለማዘመን የሚያስችል የ50 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የአርባ ምንጭ የዓዞ እርባታን ለማዘመን የሚያስችል የ50 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር ተገብቷል

አርባምንጭ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የአርባ ምንጭ የዓዞ እርባታን ለማዘመን የሚያስችል የ50 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን የጋሞ ልማት ማህበር አስታወቀ።
ማህበሩ በያዝነው በጀት ዓመት ከቱሪዝም እና ከቆዳ ሽያጭ እስከ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።
የቱሪዝም አገልግሎት፣ የብዝሃ ሀብት ጥበቃ፣ የምርምርና የስራ ዕድል ፈጠራን ዓላማ በማድረግ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የአርባ ምንጭ የዓዞ ራንች የተመሰረተው በ1976 ዓ.ም ነው።
ለ30 ዓመታት በመንግስት ሲተዳደር የቆየውን የዓዞ እርባታ (ራንች) የጋሞ ልማት ማህበር ተረክቦ ማስተዳደር ከጀመረ አንድ ዓመት የሆነው ሲሆን ማህበሩ ራንቹን ለማዘመን መጠነ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የጋሞ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዋኖ ዋሎሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ የዓዞ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ግብይት እንዲሁም የቱሪዝም ገቢ አቅምን ለማሳደግ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ ነው።
የዓዞ እርባታው ሰፊ ቁጥር ያለው ዓዞ መያዝ እንዲችል ገንዳዎችን ማስፋፋትና ለቱሪስት ሳቢ እና ማራኪ ማድረግ ከስራዎቹ መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ቱሪስቶቹ በቆይታቸው የምግብና የመጠጥ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት መናፈሻዎችን ለመገንባት እንዲሁም የዓዞ ቆዳ ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ጎብኚዎች ዓዞዎችን ብቻ ሲጎበኙ እንደነበር ጠቁመው በአዲሱ ማሻሻያም ከዚህ በፊት ያልነበሩ እንደ ዘንዶ፣ ጥንቸል፣ ኤሊ እና ሌሎች እንስሳትን በማምጣት የቱሪዝም ዘርፉን ገቢን ለማሳደግ በስፋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በጋሞ ልማት ማህበር የአርባ ምንጭ ዓዞ ራንች ኃላፊ ተወካይና አስጎብኚ አቶ አስደሳች ዳንኤል በበኩላቸው የዓዞ እርባታውን ዘመናዊ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ በመሆናቸው ሰፊ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል።
በዓዞ እርባታው በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ ዓዞዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ከእነዚህ መካከል ከ2 ሺህ 700 የሚልቁት ለቆዳ ሽያጭ የደረሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በአርባ ምንጭ የዓዞ እርባታ ጉብኝት ሲያደርጉ ያገኘናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ ሽመልስ አረጋ ዓዞን ከዚህ ቀደም በፎቶ እና በቪዲዮ ብቻ ማየታቸውን ጠቅሰው ዓዞን በአካል ለማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በዓዞ እርባታው የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቅሰው ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ያሉ የቱሪስት ፀጋዎችን መመልከትና ማወቅ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።