የኢትዮጵያ ወንዞችና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና የሚበይኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ወንዞችና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና የሚበይኑ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ወንዞችና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና የሚበይኑ መሆናቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሳዲቅ አደም ገለጹ።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅና በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትብብር "የሁለቱ የውሃ ሥርዓቶችና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነት፥ የዓባይና የቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልልን ስትራቴጂካዊ ሚና መዳሰስ" በሚል መሪ ሃሳብ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ምክክር ተካሂዷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሳዲቅ አደም፥ የዓባይ ወንዝና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና የሚበይኑ ወሳኝ ወንዞች ናቸው ብለዋል።
በዚህም በዓባይ ወንዝ ላይ የሙሉ ጊዜ መረጃ የሚያስተጋቡ ኃይሎች ኢትዮጵያን በቀይ ባሕር ጉዳይ አትናገሪ የማለት ምክንያትና መብት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረንን ቁዘማ ህዳሴ ግድብን በመገንባት መስበር ችለናል ሲሉም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የተጀመረውን ጥረት ሁሉም ዜጋ የጋራ አጀንዳ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ተመራማሪ ተመስገን ዋለልኝ(ዶ/ር)፥ አስተማማኝ የባሕር በር ማጣታችን በሎጀስቲክስና በትራንስፖርት ዘርፍ ውድ ዋጋ እያስከፈለን ነው ብለዋል።
ይህም በወጪና ገቢ የንግድ ሥርዓት ላይ ጫና በማሳደር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዳንሆን ከማድረጉ ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገታችን በሚፈለገው መልኩ እንዳይጓዝ እንቅፋት ሆኗልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን የባሕር በር መዳረሻ አለመኖር የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተባባሪ ተመራማሪ ብሌን ማሞ፥ የባሕር በር ባለቤትነት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ካለው ፋይዳ ባሻገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚፈጥረውን ዕድል ማየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ቀጣናዊ የሰላምና መረጋጋት የኃይል ሚዛንን ለማስጠበቅም የኢትዮጵያን የባሕር ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት በአስተማማኝ መሠረት መገንባት እንደሚያስፈልግም አጽነኦት ሰጥተዋል።
የዓለም አቀፍ የህግ ተመራማሪው ደጀኔ የማነ፥ የመንግስታቱ ድርጅት ኢትዮጵያና ኤርትራን በኮንፌዴሬሽን ሲያዋህድ በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር እና የወደብ ባለቤትነት እንዲካተት አድርገዋል ብለዋል።
የ2010 የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ውሳኔዎችና አጠቃላይ ሂደቶችን ታሳቢ በማድረግም በዓለም አቀፍ ሕግ ክርክር የማድረግ ዕድል እንዳላት አስረድተዋል።