ቀጥታ፡

የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና  አህጉራዊ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና በመታገዝ ምርቶቿን ለአፍሪካ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ አህጉራዊ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የአገር ውስጥ አምራቾች በስምምነቱ በመታገዝ ምርታቸውን በጥራት ለገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነታቸውን ማጉላት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር የሰው ሃብት ልማትና ድህነት ቅነሳ ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የህዝብ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ አገራት የተሻለ የገበያ እድል አላቸው።


 

በዚህ ዕድል ለመጠቀም  ከጎረቤት አገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ ትስስር መፍጠር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።  

የተፈጠረው ዕድል የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋትና ምርትን በብዛት ለማቅረብ አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ አምራቾች በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ምርት እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ከተለያዩ አገራት ጋር የገበያ ስርዓት ልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠርና የኢኮኖሚ ስርአቱን ለማቀናጀት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና በመታገዝ ምርቶቿን ለአፍሪካ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መጎልበት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው ተመራማሪው ያስረዱት።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪና ከፍተኛ ተመራማሪ መዚድ ናስር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና፣ አባል አገራት በታሪፍ ስምምነት እንዲገበያዩ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጉላት ለአገር ውስጥ አምራቾች የገበያ እድልና ትስስር ለመፍጠር፣ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትና አማራጭ የገበያ እድል ለመፍጠር አይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የተዘረጋው ስርዓት አገራት በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ ከማድረግ ባሻገር ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አስረድተዋል። 

ዓለም አቀፋ የንግድ ስርዓት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ስምምነቱ ተግባራዊ መደረጉ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል።     

የአገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን በላቀ ጥራት በማቅረብ ተወዳዳሪነታቸውን ማጉላት እንደሚጠበቅባቸው ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር)  አስገንዘበዋል።

መዚድ ናስር (ዶ/ር) በበኩላቸው አምራቾች ምርቶቻቸውን የሚልኩባቸውን አገራት ፍላጎትና አለም አቀፍ የግብይት ስርአትን በሚገባ መረዳት  አለባቸው ብለዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ስርአት ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ዲዛይንና ጥራትን በሚመለከት የተሻለ ግንዛቤ ማዳበር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ምሁራኑ አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም