ቀጥታ፡

ትምህርት ቤቶች ዕውቀት በመስጠት ትውልድን ከመገንባት ባለፈ ህይወት በመታደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው

አዳማ ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ትምህርት ቤቶች ዕውቀት በመስጠት ትውልድን ከመገንባት ባለፈ ህይወት በመታደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ የደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዓመታዊ የደም አሰባሰብ ዕቅድ ለማሳካት ከአዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ርዕሰ መምህራን ጋር በአዳማ የጋራ ፎረም እያካሄደ ነው። 


 

በፎረሙ መክፈቻ ላይ የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ እንደገለፁት በደም እጦት የሚያልፈውን የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በደም አሰባሰብ ሂደት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው። 

ባለፈው ዓመት ከ423 ሺህ ዩኒት በላይ ደም በመሰብሰብ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ህይወት መታደግ መቻሉን ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በዚህም የተማሪዎች፣ የመምህራንና ርዕሰ መምህራን ድርሻ ከፍተኛ ነበር ብለዋል። 

ትምህርት ቤቶች ዕውቀት በመስጠት ትውልድን ከመገንባት ባለፈ ህይወት በመታደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመው በተቋማቱ ያለውን ወጣት ማህበረሰብ በመጠቀም ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ለመሰብሰብ የታቀደውን 130 ሺህ ዩኒት ደም ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 550 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅደን እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም ከ120 ሺህ  በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልፀዋል።  

በሌላ በኩል በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 153 የዓይን ብሌን መሰብሰቡን ጠቅሰው ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውንም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል። 

የከፍተኛ 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሳሙኤል አሊ በበኩላቸው ደም በመለገስ ህይወት በማዳን ስራ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

አምና 350 ዩኒት ደም የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች መለገሳቸውን ጠቅሰው ዘንድሮ እስከ 600 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ እየሰራን ነው ብለዋል። 

በካቶሊክ ቅዱስ ዮሐንስ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ዲን የሆኑት መምህር ሃይለሚካኤል አፅበሃ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደም መለገስን ባህል በማድረግ በየዓመቱ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በአሁኑ ወቅት የደም መሰብሰብ ስራን ለመጀመር ከደም ባንክ አገልግሎት ሰብሳቢ ባለሙያዎችን እየጠበቅን ነው ብለዋል።

የአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እንዳልካቸው ደጀኔ በትምህርት ቤቱ ደም በመለገስ ህይወት የማዳን ስራ ባህል መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ከአገልግሎቱ የሚሰጠውን ዕቅድ ለማሳካትና የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን ደም እንዲሰጡ ለማስቻል ግንዛቤ በመፍጠር እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም