ቀጥታ፡

ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት -  አምባሳደር ፋይዛል ቸሪ ሲድሃርታ 

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ፋይዛል ቸሪ ሲድሃርታ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ መንግስት የተለያዩ ሀገራትን አዳዲስ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል። 

የሹመት ደብዳቤ ካቀረቡት አምባሳደሮች መካከል በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ፋይዛል ቸሪ ሲድሃርታ ይገኙበታል። 


 

አምባሳደር ፋይዛል ቸሪ ሲድሃርታ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በኢንዶኔዥያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እና በተለያዩ ዘርፎች እያደገ ያለ ነው። 

የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በፖለቲካው መስክ ብቻ ሳይወሰን በተጨባጭ የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፎች ውስጥም ለማሳደግ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

በተለይም በግብር ፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ቴክኖሎጂ ላይ በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በቀጣይም በግብርናው ዘርፍ፣ በግብርና ምርት ማቀነባበር እና በዓሳ እርባታ ዙሪያ የጠበቀ ትብብር ለመፍጠር እድሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የሁለቱ አገራት የንግድ ግንኙነት  የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

ለዚህም በንግድ ምክር ቤቶች መካከል ያለውን ትብብር እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በኢንዶኔዢያ አግባብነት ባላቸው ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና የኢንዶኔዥያ ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊውን መሠረት ባደረገ መልኩ በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት እና በባህል ልውውጥ ዘርፎች የበለጠ ለማደግ ከፍተኛ እምቅ አቅም አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም