ቀጥታ፡

የመረጃ ፍሰቱን በማጠናከር የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦የመረጃ ፍሰቱን በማጠናከር የምክክር ሂደቱን ውጤታማ የማድረግ ተግባር በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በወላይታ ሶዶ ከተማ "የሴቶች፣ የወጣቶች፣ እና የአካል ጉዳተኞች ሚና እና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን እንደገለጹት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው የመረጃ ፍሰቱን በማጠናከር የምክክር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ይህም መድረክ እስከ ታች ካሉ መዋቅሮች እና የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የመረጃ ፍሰት ስርዓቱን ለማሳለጥና ግንዛቤን ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑ አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም በአማራ፣ በድሬዳዋ፣ በሀረር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በሶማሌ ክልሎች ተመሳሳይ መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰው ተደራሽነቱን በማስፋት የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የመድረኩ ተሳታፊዎች የምክክር ሂደቱን ከዳር ሆነው ከመመልከት ይልቅ የወከሉትን ህዝብ ፍላጎት ተረድተው ባለቤትነቱ እስኪረጋገጥ መስራት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አካል ጉዳተኞች ተወካይ ህብስት መንክር በበኩላቸው ኮሚሽኑ በመሰል መድረኮች ሀሳባችንን እንድናቀርብ እና በአንድ ልብ እንድንሳተፍ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።


 

ግጭትና አለመመግባባቶች በሚከሰቱበት ወቅት አካል ጉዳተኞች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች እንደሚሆኑ ጠቁመው በሀገራዊ ምክክሩ የጎላ ተሳትፎ በማድረግ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማረጋገጥ እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በጦርነትና አለመግባባት አባዜ ውስጥ ለቆዩ ሀገራት ብርሃን ፈንጣቂ ነው ያለው ደግሞ የጎፋ ዞን ወጣቶች ተወካይ በኃይሉ በልጅጌ ነው።


 

በመሆኑም ህዝቡ በተወካዮቹ በኩል የሰጠውን አጀንዳ የመፈጸም ኃላፊነት በኮሚሽኑ ላይ መጣሉን አክሎ ዕድሉን በመጠቀም ለኮሚሽኑ ስራ ስኬታማነት የበኩላችንን እንወጣለን ብሏል።

በመድረኩም የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች እንዲሁም የሚዲያ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም