በጌዴኦ ዞን የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ እየተሰራ ነው

ዲላ ፤ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን የማህበረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ገለፀ።
የመምሪያው ኃላፊ ዳዊት ጀቦ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል።
የዲላ ከተማን ጨምሮ በአራት ከተሞች የጥልቅ ጉድጓድ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ማብቃትን ጨምሮ የተበላሹ 483 የውሃ ተቋማትን ጠግኖ ወደ አገልግሎት መመለስ መቻሉን አንስተዋል።
በዚህም ከ96 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ በማድረግ የዞኑን የውሃ ሽፋን ከ10 በመቶ ወደ 40 በመቶ በላይ ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በተለይ በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ገቢ የማመንጨት አቅማቸውን በማሳደግ ዘላቂ አቅርቦትን ከማረጋገጥ ባለፈ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ህብረተሰቡን እና አጋር አካላትን በማስተባበር በዞኑ ሁሉም መዋቅሮች የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃን በመጠቀም የንጹህ መጠጥ ውሃን ተደራሽ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
በዚህም በተያዘው ዓመት ከ100 ሺህ የሚልቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በዞኑ የይርጋጨፌ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰብስቤ ታምሩ በበኩላቸው በወረዳው ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 12 አዲስ የምንጭ ማጓልበትን ጨምሮ 470 የውሃ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ መደረጉ የንጹህ ውሃ ተደራሽነትን አስፍቷል።
በተያዘው ዓመት ማህበረሰብ አቀፍ የውሃ አስተዳደርን በማጠናከር ዘላቂ አቅርቦትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በወረዳው የንጹህ መጠጥ ውሃ ክፍያ ተመንን በማሻሻል ዘላቂ አቅርቦትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዲላ ዙሪያ ወረዳ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሜሪኩሪ ወልደየስ ናቸው።
በተለይ የህብረተሰብ ተሳትፎን በማሳደግ በብልሽት ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ የውሃ ተቋማት ጥገና በማድረግ ወደ ስራ መግባታቸውን ተከትሎ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የዲላ ዙሪያ ወረዳ የሚችሌ ሆላና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አማረች ገዛኸኝ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ምክንያት ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ይጋለጡ እንደነበር አንስተዋል።
ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አንስተው አሁን ላይ መንግስት የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄን በመረዳት ምላሽ እየሰጠ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።