የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ መጀመር ከእንግልት ታድጎናል - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ መጀመር ከእንግልት ታድጎናል - ተገልጋዮች

አሶሳ፤ ጥቅምት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ መጀመር ከብልሹ አሰራር እና እንግልት እንደታደጋቸው ተገልጋዮች ተናገሩ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጳጉሜን 5/2017 ዓ.ም ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
ማዕከሉ ሶስት የፌዴራል እና አምስት የክልል ተቋማትን አካቶ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በማዕከሉ ያገኘናቸው ተገልጋዮች መሶብ የምንፈልገውን አገልግሎት በአንድ ላይ እንድናገኝ ከማድረጉ በተጨማሪ ከብልሹ አሰራር ታድጎናል ብለዋል።
የንግድ ስያሜ ለማውጣት ወደ ማዕከሉ የመጣው ወጣት አባቢያ ተስፋዬ እንደተናገረው፤ በማዕከሉ ያገኘው አገልግሎት ከዚህ ቀደም ሶስት የተለያዩ ተቋማት በመሄድ ይስተናገድ የነበረበትን ሁኔታ ያስቀረ ነው።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፌዴራል ደረጃ እንደተጀመረ በአጭር ጊዜ ወደ ክልሉ በመድረስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ትልቅ ስኬት እንደሆነም ተናግሯል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲቀረፍ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን የተናገረው ወጣት አባቢያ በቀጣይ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የበለጠ ተደራሽ መሆን አለበት ነው ያለው።
ከባምባሲ ከተማ የሙያ ፍቃድ ለማሳደስ የመጡት ወይዘሮ አለሚቱ ፉፋ በበኩላቸው፤ ወደ ማዕከሉ ሲመጡ ከአቀባበል ጀምሮ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ባለጉዳይን የማጉላላት ተግባር በብዛት ይስተዋል እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን በመሶብ ማዕከል ሁሉንም አገልግሎት አግኝቻለው ብለዋል።
ማዕከሉ የዲጂታል አገልግሎት በመስጠቱ ግልጽ እና ፍትሀዊ አገልግሎት ለማግኘት አስችሎናል ያሉት ደግሞ በማዕከሉ አዲስ ንግድ ፈቃድ ለማውጣት የተገኙት አብዱልከሪም ሰላማ ናቸው።
መሶብ ከዚህ ቀደም በየተቋማቱ ይታይ የነበረውን የባለጉዳይ እንግልት በማስቀረት ፈጣን አገልግሎት በማግኘት እንድንስተናገድ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የቤጉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሰመረ ጅራታ ማዕከሉ ስራ ከጀመረ ወዲህ በርካታ ተገልጋዮችን እያስተናገደ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጥ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እንዲሟላ መደረጉን ጠቅሰው፤ ባለሙያዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረግም አስረድተዋል።